Emahoy Tirsit Eguale
የእመምኔት እማሆይ ትርሢት እጓለ አጭር የሕይወት ታሪክ የካቲት ፳፩ ቀን ፲፱፻፴፰ ዓ/ም - መስከረም ፲ ቀን ፳፻፲፱ ዓ/ም
እማሆይ ትርሢተ ሥላሴ እጓለ፤ ከአባታቸው ከሊቀ ካህናት ልሣነወርቅ ሀብተ ማርያም እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ሙሉነሽ ዘለቀ በጅባትና ሜጫ አውራጃ በግንደ በረት ካቺሲ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የካቲት ፳፩ ቀን ፲፱፻፴፰ ዓ.ም. ተወልደው ስማቸው ቀለመ ወርቅ ልሣነ ወርቅ ተባሉ። በ፹ ቀን ክርስትና ሲነሡ ደግሞ የክርስትና ስማቸው ትርሢተ ሥላሴ ተብለው ተጠሩ።
በ፮ ዓመት ዕድሜያቸው ወደ ዐዲስ አበባ በመምጣት አቶ ዕጓለ ተገኝና ወይዘሮ አዳነች ታደሰ ዘንድ በማደግ ትምህርታቸውን ጀመሩ። በልጅነታቸው ጀምሮ ለትምህርት ትጉህ እና ለመንፈሳዊ ሕይወት ቅርብ የነበሩ ሲሆን፣ በኋላም በእቴጌ መነን የእጅ ጥበብ ትምህርት ቤት ገብተው በልዩ ልዩ የእጅ ሥራዎችና በሙያ ትምህርት ሰልጥነዋል። ትምህርታቸውን በተሳካ ሁኔታ ካጠናቀቁ በኋላ የምረቃ ዲፕሎማቸውን ከቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ እጅ ተቀበሉ። በትምህርት ዘመናቸውም በሥነ ምግባር፣ በታዛዥነትና በትጋት የሚታወቁ ነበሩ።
እማሆይ ትርሢት ከልጅነታቸው ጀምሮ ለቤተ ክርስቲያን አጥብቀው የተቆራኙ ነበሩ። በጸሎት፣ በጾም፣ በአርምሞና በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በትጋት ይኖሩ ነበር። በተለይም ችግረኞችን፣ ወላጅ አልባ ሕፃናትን፣ አረጋውያንንና የታመሙ ሰዎችን በገንዘብ፣ በልብስ፣ በመድኃኒትና በመንፈሳዊ ምክር በመርዳት የብዙዎች እናት ሆነው ኖረዋል። በትሕትና፣ በፍቅርና በሰላም የታወቀ ሕይወት ኖረዋል።
እግዚአብሔር በልጅነታቸው የጠራቸው እማሆይ ትርሢት በ፲፮ ዓመታቸው ወደ ጌቴሴማኒ ሰበታ ገዳም ገብተው የምንኩስና ሕይወትን ጀመሩ። ከአመክሮ በኋላ ቅድስናን፣ ድኽነትንና መታዘዝን መርጠው ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር ሰጡ። በኋላም በደብረ ሊባኖስ ገዳም በምንኩስና ሥርዓት ተቀብለው “እማሆይ ትርሢተ ሥላሴ” ተብለው ተሰየሙ። በምንኩስና ሕይወታቸውም ከስድሳ ዓመታት በላይ በጸሎት፣ በጾም፣ በአርምሞና በአገልግሎት ኖረዋል።
በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ፈቃድ ወደ ጀርመን ለትምህርት ተልከው ከቆዩ በኋላ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሄዱ። ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ገዳማቸው ተመልሰው በእመምነትነት አገልግለዋል። በኋላም በእንግሊዝ በነበራቸው ቆይታ ለብዙ ምእመናን መንፈሳዊ ድጋፍና ምክር በመስጠት ታላቅ አገልግሎት አድርገዋል።
እማሆይ ትርሢተ ሥላሴ ከረጅም ዓመታት የጸሎትና የአገልግሎት ሕይወት በኋላ ወደ ውድ ሃገራቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በሰበታ ጌቴሴማኒ ገዳም ሳሉ በመስከረም ፲ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም. (20 September 2026) በሰላም አረፉ። በዚያው በሰበታ ጌቴ ሴማኒ ቤተ ደናግል ገዳም ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል። እናታችን እማሆይ ትርሥተ ሥላሴ ለቤተ ክርስቲያን ያበረከቱትን የእምነት፣ የትሕትናና የፍቅር ቅርስ ትተውልን አልፈዋል።